በአምባገነኖች ዛቻ እና ማስፈራሪያ የመብት ጥያቄ እና የነፃነት ትግል አይቆምም!

በከልለው ኡርጋ*

EnoughWithTPLF20152

በምስራቅ አፍሪካ በመብት ጥሰት አቻ ያልተገኝላት፣ አምባገነኖች በንፁሀን ሕዝቦች ላይ ያሻቸውን አፈና፣ እንግልት፣ ግድያ፣ እስር፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያገዘፉ እና እያበራከቱ የመጡባት ብቸኛዋ ሀገር – ኢትዮጵያ ናት። ሲፈልጉ ወገኖቻችንን በተናጠል ያፍናሉ፣ ያስራሉ፣ ይገድላሉ። በሌላም ጊዜም፣ በጅምላ ይጨፈጭፋሉ። ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስልጣኑን በበላይነት ይዘው እና ተቆጣጥረው፣ የፈለጉትን እና ያሻቸውን ያደርጋሉ። የሀገራችንን ሀብት ከመሟጥሟጣቸውም በላይ፣ ትልቁ ንቀታቸው፣ የተወሰኑትን የስርዕቱ አቀንቃኞች ለመጥቀም፣ በሚሊዮን የሚቆጠረውን ጭቁኑን የኦሮሞ አርሶ-አደር ሕዝብ ከቀዬው ለማፈናቀል እና ማንነቱን ለማጥፋት በማቀድ እና በማሴር ከግብ ሊይደርሱ ማሰባቸው ነው።

ሕዝብን ይዘልፋሉ፣ ያስራሉ፣ ይገርፋሉ፣ ይገድላሉ – አምባገነኖቹ!

በአንድ ወቅት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስርዓቱ በፈጠረው ምክንያት ስራ-አጥ ወጣቱን “አደገኛ ቦዘኔ” በማለት በመሳደባቸው፣ ውጤቱ ምን እንደነበረ በ97ቱ የምርጫ ወቅት በሚገባ አምባገነኖቹ አይተውታል። ዛሬ ደግሞ፣ የአምባገነኖቹ ቁንጮ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል እና የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ አቶ አባይ ፀሐዬ “ልክ እናስገባቸዋለን!” የሚለው ዛቻ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ሳይገነዘቡት ቀርተው አይመስለኝም። አቶ አባይ ፀሐዬ ከ40 ሚሊያን በላይ ከሚገመተውን ከኦሮሞ ሕዝብ፣ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያየዞ የተናገሩት ንቀት ያዘለ ዛቻቸው የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ አምባገነኖች እንደሆኑ ሳይውል ሳያድር የሚያዩት ጉዳይ ይሆናል። በኦሮሞ ሕዝብ ማንነት እና ህልውና ጉዳይ ላይ ለተሰነዘረው እና ለተቃጣው ዛቻ እና ማስፈራሪያ፣ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ዛሬ በአምባገነኖች ዛቻ እና ማስፈራራት የሚበረከክ ትውልድ ሳይሆን፣ ጨቋኞቻችንን የሚያንቀጠቅጥና ለሕዝብ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ታላላቅ ጀግኞች እና ብዙ “ሞት አይፈሬ” ወጣት ትውልድ የተፈጠረበት ዘመን ነው።

በተለያየ ጊዜም፣ ይህ የታየበት ሁኔታ አለ። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ጨምሮ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመቃወም፣ ወጣቱ ቁርጠኝነቱን እና ጀግንነቱን አሳይቷል። ምንም እንኳን አምባገነኖች በግፍ ላይ ግፍ በወንጀል ላይ ወንጀል መደራረብ የለመዱ ቢሆንም፣ የተጨቆነው ሕዝብ የግፍ አገዛዝ ‘አይበቃም ወይ’ እያለ ያለበት ዘመን ነው። በማንነት እና በህልውና ላይ ለተቃጣው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ለአምባገነኖቹ ማፈሪያ እና ውድቀት እንጂ ለተበደለ፣ ለተከፋ፣ ለተጨቆነ፣ ለታፈነ እና ለተበዘበዘ ደግሞ የበለጠ ለነፃነቱ ትግል የሚያነሳሳ ነው። ትውልዱ ያደረገው እና እያደረገው ያለው ተጋድሎ፣ የከፈለው እና እየከፈለ ያለውን መስዋትነት ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። አሁንም የተቃጣብንን የማንነት-ማጥፋት ዘመቻ ለመመከት ከምን-ጊዜም በጠነከረ መልኩ በተመሳሳይ የአምባገነኖቹ ግፍ እየደረሰበት ካሉ ሌሎች ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ለትግሉ ቁርጠኝነት ያሳየበት ወቅት ነው።

በዚያች ሀገር ለመኖር የግድ የገዝው ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ መሆን ያስፈልጋል፤ ያልሆነ ግን በጥርጣሬ ይታያል። የአገር ሀብት አትመንዝሩ፣ መልካም አስተዳደር ይምጣ፣ የዲሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፣ ለህግ ተገዢ ሁኑ ብሎ የገዥውን ፓርቲ በግልፅ የሚናገር ወይም የሚመክር ግለሰብም ሆነ ድርጅት ደግሞ ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሕዝብ፣ ፀረ-ዲሞክራሲ የሚል ታፔላ ይለጥፉለታል። በዚህም አያበቁም አፍነው ይገድላሉ ወይም በሐሰት ክስ ወደ ከርቸሌ ወይም ወደ ዘብጥያ ያወርዳሉ።

በዚያች ሀገር ሰላምን እና ነፃነትን ለማምጣት እና ለመኖር የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ከተጨቆኑ እና በተመሳሳይ ያአምባገንኖች የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሻቸው ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ከጎኑ አሰልፎ እና ተባብሮ አንድ ወጥ ትግል ታግሎ በመጀመሪያ ጨቆኙን እና አምባገነኑን ወያኔ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው። አምባገነኑ የወያኔ መንግስት ከተወገደ በኋላ ለሁሉም፣ የምትስማማ ሰብዓዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና የሕግ የበላይነት የሚከበርበት ምቹ ሀገር መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው ልክ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሻቸው ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጎን በመቆም መታገል ሲችሉ ብቻ ነው።

ድል ለኦሮሞ ሕዝብ!

* ከልለው ኡርጋ:- kiyu297@gmail.com

Source- Gadaa.com

Posted By- Zenebu Gebreu

Leave a comment