ቦሩ በራቃ:- ከኣቶ ያሬድ ጥበቡ ኦሮምያን ለሁለት የመግመስ ነፍጠኛዊ ‘ጥበብ’ በስተጀርባ

በቦሩ በራቃ*

ስማቸው የተጠቀሰው ኣዛውንት ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ በወጣትነታቸው የተካፈሉ ናቸው። ሁዋላ ላይ ግን ከተሰለፉበት ሃይል ተለይተው፣ ጉዋዶቻቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሲሆኑ እርሳቸው ስደት ላይ መሆናቸውን የግል ድረ-ገጻቸው ላይ ይነግሩናል። ኣቶ ያሬድ ጥበቡን ለማስተዋወቅ ጊዜዪን የማባከን ግዴታ የለብኝም። ባጭሩ ግለሰቡ ቀደም ሲል ወያኔ ዛሬ ደግሞ ኣደገኛ ኒዮ(Neo)-ነፍጠኛ መሆናቸውን በየመጣጥፎቻቸው ሁሉ የሚያንፀባርቁት ኣስተሳሰባቸው እየነገረን ነው። የሚገርመው ደግሞ ኣልፎ ኣልፎ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሲያገኙ እኔኮ እገሌ የሚባለው የኦሮሞ ዘር ነኝ እያሉ ማወናበድም ይታይባቸዋል። ለነገሩ በዛሬው ዘመን የምናያቸው የነፍጠኛው ስርእት ኣቀንቃኞች ወጣት ኣዛውንት ሳይለይ ኣንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ይሄው የተነቃበት ስልታቸው ነው። ኦሮሞን ለማታለል ሲከጅሉ ‘እኔምኮ በኣባቴ ወይም በእናቴ ኦሮሞ ነኝ’ ኣይነት ኣሰልቺ ፈሊጥ ተያይዘዋል።

ዛሬ ትኩረቴን የሳበው ኣቶ ያሬድ ጥበቡ ሰሞኑን ‘ምን ይሻላል?’ በሚል መጠይቃዊ ርእስ የፃፉት ጉዳይ ነው። በዚህ ፅሁፋቸው የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን በመሰሎቻቸው ዘንድ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የኖረን ውጥን ገሃድ ስላወጡት ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ ሆኖ ኣገኘሁት። እናም ይህ ፅሁፍ ያነጣጠረው በዋነኝነት ለኣቶ ያሬድ ጥበቡ ስብእና ክሬዲት ለመስጠት ሳይሆን እንደ እሳቸው ሁሉ ከኣንድ ኣይነት የትምክህት ፋብሪካ ተፈብርከው ኦሮሞነትና ኦሮምያን ለማጥፋት ደቦ ለሚጠራሩት ሁሉ ምላሽ እንዲሆን ነው።

እነ እቶ ያሬድን በጣም ኣስጨንቆኣቸውና ኣስጠብቦኣቸው ‘ምን ይሻላል?’ ያስባላቸው ኦሮምያ በፍንፍኔ ላይ ያላት የባለቤትነት መብት ጉዳይ ነው። ወያኔ ካልተገበርኩት ብሎ የፎከረውን “የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን” በተመለከተ ነው የነኣቶ ያሬድ ጭንቀት። ታዲያ ግለሰቡ ‘ምን ይሻላል?’ ብለው ፅሁፋቸውን መጀመራቸውን ብቻ ያየ የዋህ ሰው ምናልባት እኒህ ሽማግሌ የኦሮሞ ህዝብ በማስተር ፕላኑ ሳቢያ ከቀዬው ላይ የመፈናቀሉ ጉዳይ ኣሳስቦኣቸው የኣረጋዊነት ኣስታራቂ ኣስተዋፅኦ ለማበርከት ኣስበው ይሆን ብሎ መጠየቁ ኣይቀርም። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። የነፍጠኛውን ተጠባቢ ያሬድ ጥበቡን ያስጠበባቸው እንዴት ኦሮሞ በሸገር ላይ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳል የሚለው እንጂ የኦሮሞ በገዛ ኣገሩ ላይ መበደልና መገፋት ኣይደለም። ታዲያ ኣሃዱ ብለው ፅሁፋቸውን የጀመሩትም እንዲህ በማለት ነበር።

“የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በብዙ ጉዳዮች የሚለያዩ ቢሆንም፣ ፊንፊኔ መናገሻችን ናት በሚለው ጉዳይ ግን ይስማማሉ። ለዚህም ይመስላል በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ፣ ኦሮሞ ፈርስትና ኦፒዲኦ እጅና ጓንት ሆነው ሃገሩን ያተራመሱት። ለመሆኑ ፊንፊኔ የኦሮሞ መናገሻ ነበረች? ኦሮሞዎች ከየት መጡ?”

በዚህ ኣባባላቸው ሁለት ድንጋዮችን ኣንስተው ኦሮሞ ላይ ወርዉረዋል፣ ግለሰቡ። ኣንደኛው፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነቶች እያሏቸው ነገር ግን ኣንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ መገኘቱ ኣቶ ያሬድን በጽኑ እንዳበገናቸው ከዚህ ኣባባላቸው እንረዳለን። ሌላው ደግሞ ግለሰቡን ክፉኛ የወገራቸው የነፍጠኝነት ጠኔ ኦሮሞ ኣገሩ እዚህ ኣይደለም የሚለው የበሰበሰና የበከተ የኣባቶቻቸው ተረት ተረት ነው። ለዚህም ነው ‘ለመሆኑ ፊንፊኔ የኦሮሞ መናገሻ ነበረች? ኦሮሞዎችስ ከየት መጡ?’ እያሉ ቆርፋዳ ጥያቄ የሚያነሱት።

ኣቶ ያሬድ የኣባቶቻቸውን ስልት በመከተል ኦሮሞን በኦሮሞ ለመምታትም ሞክረዋል። መርዛቸውን ለመትፋት ዋቢ መጥራት የፈለጉት የፊውዳል-ነፍጠኛ ስርዓትን ሲያገለግሉ የኖሩት የይልማ ዸሬሳን ቅዠታዊ ድርሰት ነው። ስለ ኣቶ ይልማ ዸሬሳ ማንነት ለጊዜው ኣሁን ማንሳት ኣልፈልግም። ኣቶ ያሬድ ይቀጥላሉ። ዋነኛ መከራከሪያቸውም ኦሮሞ ኣገሩ ኣሁን ካለበት መሬት ላይ ኣይደለምና የፍንፍኔን የባለቤትነት መብት እርግፍ ኣድርጎ መተው ኣለበት ነው። እኛ እዚህ ኣካባቢ ላይ የ3000 ኣመት ታሪክ ሲኖረን እናንተ ኦሮሞዎች ግን 500 ኣመት ኣልደፈናችሁም ሊሉን ዳድተዋል። እዚህ ጋር ሳቄ መጣ። የ3000 ኣመቱን የጥንታዊት ኩሽ-ላንድን (ኦሮሞና ኑቢያን ያካተተ) ስልጣኔ ሴማዊያኑ ሃበሾች ትላንት ከደቡብ ኣረቢያ ፈልሰው መጥተው በመንጠቅ የታሪኩ ባለቤት የሆነውን የኩሽ ታላቁ ግንድ ኦሮሞን ኣገርህ እዚህ ኣይደለም ሲሉት መሳቅ ነው ኣንጂ የምን መገረም! በመጽሃፍ ቅዱስ ሁሉ ሳይቀር በእብራይስጥ ቁዋንቁዋ ‘Cush shall soon stretch her hands unto God’ የተባለውን ይሉኝታ-ቢሶቹ ሃበሾች ጠምዝዘውት ባለታሪኮቹን ኩሾች ወደ ጎን በመተው ራሳቸውን የስልጣኔ ማማ ላይ ማስቀመጣቸውና ‘እኛኮ ስማችን መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይቀር የተጠቀሰ ክቡር ዘሮች’ ነን ሲሉ ነው የሚያስቀኝ። ታላቁ ኣባታችን የሚሉት ዳግማዊ ምኒልክ ‘እኔ ኣፍሪቃዊ ወይም ከጥቁር ነገድ ኣይደለሁም’ በማለት እሱና ዘር-ማንዘሩ ለከተሙበት ሸገርም ሆነ ኣገር እንግዳ መሆናቸውን በራሱ ኣንደበት ሲመሰክር ኣልሰሙም ወይም ኣላነበቡም ይሆናል ጠቢብ ነኝ ባዩ የኣቶ ጥበቡ ልጅ።

Gadaa.com

posted zenebu gebru

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s