“ልጆቼም እኔም ፍትህ እንሻለን”

 

“ልጆቼም እኔም ፍትህ እንሻለን”

(የሟች ኢ/ር ጀሚል ባለቤት፤ ወ/ሮ ፋጡ የሱፍ)
“ለመጀመሪያ ጊዜ የባሌን መታመም በስልክ ነው የሰማሁት፡፡ ሌላ ጊዜ ወገቡን ያመው ስለነበር ያው ህመሙ ነበር የመሰለኝ። ተኝቷል ወደተባለበት አሚን ጀነራል ሆስፒታል በፍጥነት ስሄድ ያጋጠመኝ ሌላ ታሪክ ነው፡፡ ባለቤቴ ጭንቅላቱ ተጐድቷል፤ አንድ የቀረ የሰውነት ክፍል የለውም፡፡ ተደብድቧል፡፡ ራሱን ስቶ እየቃዠ ነበር ያገኘሁት (… ከፍተኛ ለቅሶ …) ነገሩን ሳጣራ በብዙ ሰዎች ተደብድቦ ከቡታጅራ ነው ወደ አሚን ጀነራል ሆስፒታል የመጣው”
ይሄን የተናገሩት ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም የ“ሊቃ” በዓልን ለማክበር ወደ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ፣ ሚኬኤሎ ገበሬ ማህበር፣ መልካሜ መስጊድ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ሄደው፣ ባደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው ያለፈው የኢ/ር ጀሚል ሀሰን ባለቤት ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ ናቸው፡፡ በጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ በየወሩ የሚከበረውን “ሊቃ” የተሰኘ ሀይማኖታዊ በዓል ለማክበር ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሱማሌ ተራ ከሚገኘው መስጊድ ተነስተው ከ50 በላይ ሰዎች ወደ ስፍራው ተጉዘው ነበር፡፡ በእለቱ ሚኬኤሎ በተባለው አካባቢ መልካሜ መስጊድ ደርሰው ስርዓቱን ለመከታተል ገና እንደገቡ እጅግ በርካታ ዱላ የያዙ ሰዎች ከአዲስ አበባ የሄዱትን ሰዎች መደብደብ ጀመሩ። አገር ሰላም ብለው የሄዱት እንግዶች፤ በአካባቢው ሰው የዱላ ውርጅብኝ ሲወርድባቸው ያመለጠው አመለጠ፤ የተጐዳው ተጐዳ፤ ነገር ግን ኢ/ር ጀሚል ማምለጥ ባለመቻላቸው ዱላው ሁሉ ሰውነታቸው ላይ አረፈ። ጭንቅላታቸውም ላይ ድንጋይ ተጫነ፡፡ በሞትና በህይወት መሀል ሆነው ከአዲስ አበባ በተላከ አምቡላንስ አሚን ጀነራል ሆስፒታል ገቡ፡፡
ህይወታቸውን ለማትረፍ ዶክተሮችና ነርሶች አቅምና እውቀታቸውን እስከመጨረሻው አሟጠው ቢጠቀሙም የኢ/ር ጀሚል ህይወት ተስፋ ሰጪ አልነበረም፡፡ በአስቸኳይ ወደ ቱርክ ሄደው እንዲታከሙ የአሚን ጀነራል ሆስፒታል ዶክተሮች ትዕዛዝ አስተላለፉ። ጉዞ ወደ ቱርክ ሆነ፡፡ ቱርክ በደረሱ በሶስተኛው ቀን ኢ/ር ጀሚል ሀሰን ይህቺን አለም እስከወዲያኛው ተሰናበቱ። “በሰው አገር ደህና ሰውነት የሌለውን፣ በዱላ ባዘቶ የሆነውን የባሌን አስክሬን ይዤ ግራ ገባኝ፤ ልጆቼን አሰብኳቸው፤ ለልጆቼ አባታቸው ምን ማለት እንደሆነ የማውቀው እኔ ነኝ” ይላሉ፤ የአቶ ጀሚል ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ የሱፍ፡፡ “ልጄ ኪናን ጀማል በትምህርቱ ጐበዝ ነበረ፤ ኢትዮጵያን ወክሎ ቱርክ በመሄድ ተወዳድሮ አንደኛ በመውጣቱ ከኢስታምቡል ፓርላማ ሽልማት ተቀብሏል፤ አሁን ግን በአባቱ ሞት የተነሳ መማር አልቻለም” ብለዋል፤ ወ/ሮ ፋጡማ፡፡
የድርጊቱ መንስኤ
ወልቄጢ አካባቢ “ቃጥባሬ” የተሰኘ መስጊድ ይገኛል፡፡ መስጊዱ በኢ/ር ጀሚል ገዳይ ቅድመ አያት በሀጂ ኢሳ እንደተሰራ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ሀጂ ኢሳ በአካባቢው እስልምናን ያስፋፉ አስተማሪና በአካባቢው ህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ሼክ እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ፡፡ ሀጂ ኢሳ ካለፉም በኋላ ልጃቸው ሻለቃ ሱልጣን ሀላፊነቱን ተረክበው የእስልምናን እምነት በትክክለኛው መንገድ ሲያስተምሩ፣ የተጣላን ሲያስታርቁ፣ ለታመመ ሲፀልዩና ሲያድኑ የቆዩ የሀይማኖት አባት እንደነበሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአካባቢው ሰዎች ይናራናሉ፡፡ እኚህ አባት በስልጤ፣ ጉራጌ፣ በሶዶ ወረዳ የተለያዩ መስጊዶችን በማሰራት እምነቱ በትክክለኛው መንገድ እንዲቀጥል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ማለፋቸውን ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለፃ፤ ሀይማኖቱ እየተበላሸና ሌላ መልክ እየያዘ የመጣው ከሻለቃ ሱልጣን ልጅ እና ከልጅ ልጃቸው በኋላ ነው፡፡ በተለይ የልጅ ልጃቸው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ ከቅድመ አያቶቻቸውና ከአያቶቻቸው የተረከቡትን የእምነት ስርዓት ወደ ጐን በመተው፣ “ከአላህ ይልቅ እኔን አምልኩ” በሚል ወደ ጥንቆላና ባዕድ አምልኮ ቀየሩት ይላሉ፤ ነዋሪዎቹ፡፡ ይህን ጉዳይ አጥብቀው ከሚቃወሙት ውስጥ ደግሞ የሰልማን ሰይድ ፋሪስ አጐት በድሩ ሱልጣን አንዱ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በድሩ ሱልጣን፤ የሰልማን ሰይድ ፋሪስ የአባታቸው ወንድም (አጐታቸው) ናቸው፡፡
“ይሄ ነገር አይሆንም፤ ሰው ሁሉ ማመን ያለበት በፈጣሪው በአላህ ነው፤ ወደ አላህ መንገድ መመለስ አለብህ እያልኩ ሰው ሁሉ እሱን እንዲያመልክ የሚያደርግበትን መንገድ እቃወም ነበር፤ በዚህ ነው ሊገድለኝ የነበረው” ይላሉ፤ ከሞት የተረፉት አጐቱ አቶ በድሩ ሱልጣን፡፡ መጀመሪያ ሊገደሉ እቅድ የተያዘባቸው አጐቱ አቶ በድሩ ሱልጣን እንደነበሩና ግንቦት 19 ቀን 2004 ዓ.ም እራሱን “የሀይማኖት መሪ” እያለ የሚጠራው አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ ለታናሽ ወንድማቸው እና ለተከታዮቻቸው መመሪያ ሲያስተላልፉ ሰምቻለሁ ብለዋል – አንድ የአይን እማኝ፡፡
የቡታጅራና የአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ ህዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም (ኢ/ር ጀሚል ሐሰን ከተገደሉ ከስድስት ወራት በኋላ) የግድያው ዋና መሪ፣ አዘጋጅና አዛዥ እንዲሁም የግድያው ቀድሞ ጀማሪዎች የሀይማኖት መሪ ናቸው በተባሉት:- ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ሱልጣን፣ ወንድማቸው ነሲቡ ፋሪስ ሱልጣን፣ ወልዩ ቦንሰሞና ሁሴን አብደላ በተባሉት ተከሳሾች ላይ በሶስት ተደራራቢ ወንጀል ክስ ተመስርቶ እንደነበር የአቃቤ ህግ መዝገብ ያስረዳል፡፡ ክሱም ከባድ የነፍስ ግድያ፣ በከባድ የነፍስ ግድያ ሙከራ እና ታስቦ የሚፈፀም የንብረት ማውደም የሚል ሲሆን ተከሳሾቹ የፈፀሙት ወንጀል፤ (በሁለት ተደራራቢ ክሶች) ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚደርስ ፍርድ የሚያሰጥ ቢሆንም በቅጣት ማቅለያ ከ20 እስከ 11 ዓመት እስር ተፈረደባቸው፡፡ ክስ የቀረበባቸው 22 ሰዎች ቢሆኑም ሁለቱ አቃቤ ህግ አላስመሰከረባቸውም በሚል በነፃ ሲሰናበቱ፣ 20ዎቹ እንደየጥፋታቸው መጠን እስር ተፈረደባቸው – ከ11-20 ዓመት፡፡
የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪና አቃቤ ህግ ግን በፍርዱ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ጥፋተኞቹ ሞት እና እድሜ ልክ እስር ሊፈረድባቸው ሲገባ ፍ/ቤቱ የሰጠው ብያኔ አግባብ አይደለም ያለው አቃቤ ህግ፤ ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ጠየቀ፡፡
በቡታጅራና አካባቢው የህግ ባለሙያ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቁ ጠቁመው፤ ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች በፊናቸው ምድብ ችሎት ሆሳዕና እያለ፣ እነሱ ግን ሀዋሳ በመሄድ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ማለታቸው አግባብ አልነበረም ይላሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የጥፋተኞችን ፋይል ከፍቶ ጉዳያቸውን ካየ በኋላ፣ የቡታጅራና አካባቢው ጠ/ፍ/ቤት አቃቤ ህግ ሆሳዕና ምድብ ችሎት ይግባኝ ያለበትን መዝገብ አጣምሮ ለማየት የሟች ጉዳይ መዝገብም ወደ ሀዋሳ ተዛወረ፡፡ የጉዳዩ ሂደት መዝገብ እንደሚያሳየው፤ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት በአቶ ታረቀኝ አበራ አይዶ እና በሌሎች ዳኞች የታየው የሁለቱ ወገኖች ይግባኝ የሟችን መዝገብ በዝርዝር ሳይመለከት እንዲሁም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ የተባሉበትን ከፍተኛ የነፍስ ግድያ ወንጀል ተራ አምባጓሮ ወደሚለው በመለወጥ፣ “ከአዲስ አበባ ሊቃችንን ሊያበላሹ ይመጣሉ፤ ዱላ (ሽመል) ይዛችሁ ደብድቧቸው፣ ይህን ያላደረገ ከእኔ ጋ እንደተጣላ ይቁጠረው” የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ ግድያውን በቀጥታ መርቷል በሚል 14 ዓመት የተፈረደበትን ሰልማን ሰይድ ፋሪስ፤ አቃቤ ህግ ማክበጃ አላቀረበም በሚል በቅጣት ማቅለያ ወደ አምስት አመት፣ የግድያውን ሂደት ዱላ በማሳረፍ አስጀምሯል የተባለውና የሰልማን ሰይድ ፋሪስ ታናሽ ወንድም የሆነው ነሲቡ ፋሪስ ከ19 ዓመት ወደ ዘጠኝ አመት ሲቀነስላቸው፤ የሌሎቹም ከ13 እና ከ11 ዓመት ወደ አንድ አመት ከስምንት ወር በመቀነሱ በጠቅላይ ፍ/ቤቱ ውሳኔ፣ እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ አመት ከስምንት ወር ያለፋቸው 14 ሰዎች በነፃ ሊለቀቁ ችለዋል። ይህም ውሳኔ በሟች ቤተሰብ ዘንድ ለቅሶና ዋይታን ፈጥሯል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸውና ሂደቱን ሲከታተሉት እንደነበር የገለፁልን የህግ ባለሙያ፤ ጉዳዩን የስር የቡታጅራና አካባቢው ፍ/ቤት፤ ተንትኖ እንዳየው፤ ከ50 በላይ የሰነድና ከ50 በላይ የሰው ማስረጃ ቀርቦለት በትክክል መወሰኑን ይናገራሉ፡፡ ይህን ውሳኔ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ በአንድ አንቀፅ መሻሩ ፍትህ መዛባቱን እንደሚያሳይ የህግ ባለሙያው ገልፀዋል፡፡
“አጠቃላይ የሂደቱ መዝገብ እጄ ላይ ስላለ በደንብ ተመልክቼዋለሁ” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኢፌዲሪን የቅጣት አወሳሰን መመሪያ የጣሰ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ባለሙያው “ስህተት” ነው ያሉት 539 1(ሀ) ከፍተኛ የነፍስ ግድያ ወንጀል ወደ 540 ተራአምባጓሮ መቀየሩን ነው። ከተቀየረም የተቀየረበት አጥጋቢ ምክንያት መኖር ነበረበት፤ ነገር ግን “ይህን አልተቀበልኩም፣ ይሄ አያስኬድም” እያለ ጠ/ፍ/ቤት የወሰነው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት እንዳለበት በግልፅ ያሳያል ብለዋል፡፡
የሟች ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ የሱፍ በበኩላቸው፤ በጠ/ፍ/ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ በእርሳቸውም ሆነ በልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ሀዘን እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡ “አባቴን የገደለው ሰው አምስት አመት ከተፈረደበት እኔም እሱን ገድዬ አምስት አመት መታሰር አያቅተኝም” በሚል ልጄ ወደበቀለኝነት ሀሳብ ገብቷል ሲሉ “የፍትህ ያለህ” ብለዋል፡፡ “እኔም ሆንን ልጆቹ ኢትዮጵያዊያን ነን ልጆቼን የት ሄጄ ላሳድግ የልጄን ሀዘንና የበቀለኝነት ስሜት እንዴት ነው የማስወግደው?” በማለት ያለቅሳሉ፡፡
“ትክክለኛ ፍርድ አገኛለሁ ብዬ ከአዲስ አበባ ሀዋሳ 35 ጊዜ ተመላልሻለሁ፤ እዛም ደርሼ ለሌላ ጊዜ ተዛውሯል፣ ከሰዓት ነው እየተባልኩ ልጆቼንና ስራዬን ጥዬ ተንከራትቻለሁ” ያሉት ወ/ሮ ፋጡማ፤ በውሳኔው በጣም ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ “የጠ/ፍ/ቤቱን ፕሬዚዳንት አነጋግሪ ተብዬ አቶ ታረቀኝን እያለቀስኩ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር” ያሉት ወ/ሮዋ፤ “ትክክለኛ ፍርድ ታገኛለሽ፤ መዝገቡ በእኔ እጅ ነው” ብለውኝ ስጠብቅ፣ ጭራሽ 14 ሰዎች በነፃ ሲለቀቁ፣ የነፍሰ ገዳዮቹ ቅጣት ወደ አምስትና ዘጠኝ አመት መቀነሱ አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡
“ውሳኔው ከአድልዎ፣ ከአምቻ ጋብቻ የፀዳ ነው”
አቶ ታረቀኝ አበራ
በጉዳዩ ዙሪያ ሀዋሳ ቢሯቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አበራ፤ “ጉዳዩን በደንብ አውቀዋለሁ፤ ውሳኔውም በትክክል ታይቶ ተፈትሾ የተወሰነ ከአድልዎ፣ ከአምቻ ጋብቻ የፀዳ ነው” ብለዋል፡፡ ሆሳዕና ምድብ ችሎት እያለ፣ አቃቤ ህግም በሆሳዕና ይግባኝ ብሎ ሳለ ጥፋተኞቹ ወደ ክልሉ ጠ/ፍ/ቤት መጥተው ይግባኝ ሲሉ ፋይል ተከፍቶ መስተናገድ ነበረባቸው ወይ? በሚል ላነሳነው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “መንግስት በየአቅራቢያው ምድብ ችሎቶችን የከፈተው ሰዎች የጊዜ፣ የገንዘብና መሰል ብክነቶች ለመከላከል ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሆኖም ለየት ያሉ ጉዳዮች ሲመጡ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፋይል እንደሚከፍት ገልፀው፤ ይሄኛውን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ሀይማኖታዊ ይዘት ስላለው ነው ይላሉ፡፡ አንቀፁ ከ539 /ሀ/ (1) እንዴት ወደ 540 (ተራ አምባጓሮ) ወደሚለው ለምን ተቀየረ? በሚል ላቀረብነው ጥያቄም፤ “ጉዳዩ የተፈፀመው በሀይማኖት ቦታ ሆኖ በድንገት በተነሳ ግርግር እንጂ የታሰበበት እንዳልሆነ ፍ/ቤቱ አጣርቷል፤ በዚህም ውሳኔ ሰጥቷል” ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የስር የቡታጅራ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ተከታዮቹን በመልካሜ መስጊድ በ19/09/2004 ዓ.ም ሰብስቦ “ነገ-ከአዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች አሉ፤ የሊቃ ስርዓቱን ለማበላሸት ስለሆነ ጅሀድ (ጦርነት) እናውጅባቸዋለን፡፡ ሁላችሁም ዱላ ሽመል ይዛችሁ ቀጥቅጣችሁ ግደሉ” ስለማለቱ 50 የሰው፣ 50 የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ “አቶ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ ከዚህ ቀደም ብዙ የግድያ ሙከራዎች አድርጓል” የሚሉት አንድ የቡታጅራ አካባቢ ነጋዴ ስለተፈጠረው ነገር በደንብ እንደሚያውቁና በቅድሚያም ድርጊቱን እንደሚያወግዙ በመግለፅ ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት፡፡ ከዚህ በፊት ወንጀለኛው (ሰልማን ሰይድ ፋሪስ) በሀይማኖት ሽፋን ህብረተሰቡን ያለ አግባብ “የሀይማኖት መሪ ነኝ” በማለት ራሱን ሰይሞ ምንም የሀይማኖት ምልክት በሌለበት እየበዘበዘ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ “ሰውንም ወዳልተፈለገ እምነትና ጥንቆላ ከቶታል” የሚሉት ነጋዴው፤ ይህ ሰው ከአቶ ጀሚል በፊት በጠራራ ፀሀይ ሁለት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላይ ሽጉጥ መተኮሱን፣ በዚህም ክስ እንደተመሰከረበት ጠቁመው “የሀይማኖት መሪ ነው” በሚል በነፃ መለቀቁን ይናገራሉ። “የወረዳው ይህን ያህል ሽፋን መስጠት አሁን ወደ ነፍስ ግድያ አሸጋግሮታል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሊቃ ስርዓት በሰላም ነው በየወሩ ሲከበር የነበረው ያሉት እኚህ ግለሰብ፤ “ከአዲስ አበባ የሚመጡ ስርዓቱን የሚያበላሹ ሰዎች ስላሉ በሰላም እንዳይመለሱ በዱላ ደብድባችሁ ግደሉ” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉንና በዓሉ በሚከበርበት ቀን እርሱ በበዓሉ ላይ አለመገኘቱን፣ ከዚያ በፊት ግን ከሊቃ ስርዓቱ ቀርቶ እንደማያውቅ መስክረዋል፡፡
“አሁንም ቢሆን ማረሚያ ቤት ሆኖ በየጊዜው በመኪና እየታጀበ ወደ ቤቱ ይሄዳል፣ ኦሮሚያ ክልል ላይ የእርሻ ማሳ አለው፤ እርሱን ሊያሰራ ይሄዳል” ያሉት ግለሰቡ፤ ይህ የሚደረግለት ሽፋን ለቀጣይ ነፍስ ግድያ ያበረታታዋል ብለዋል፡፡ “ድብደባውን እና ግድያውን ፈፅመው ሲመለሱ ሌላው ተባባሪ የዛሬው ግንቦት 20 የድል ቀን ነው በደንብ አክብረነዋል እባክሽ ቅቤ ቀቢኝ ብሎ ለዋርሳው ሲናገር በጆሮዬ ሰምቻለሁ” የሚሉት ግለሰቡ፤ “ይህ ሰው ታስሮ ነበር፤ በይግባኙ ሂደት ተለቆ ወጥቷል ግን ድጋሚ እየተፈለገ ነው፤ ለአካባቢው ስጋት ሆኗል” ብለዋል፡፡
“በአካባቢያችን አንድ አርሶ አደር በቀን 60 ብር እየተከፈለው በሚሰራበት ወቅት ብዙ አርሶ አደሮች በነፃ እርሱን ሲያገለግሉ ይውላሉ” በማለትም አክለዋል፡፡
“በድሩ ሱልጣን የተባለው አጐቱ ሌሎች እንግዶችን ከአዲስ አበባ ይዞ እንደሚመጣ ያውቅ ነበር፤ አቶ በድሩ የተማረ በመሆኑ አጥብቆ ይቃወመዋል፤ ህዝቡን የሚበዘብዝበትን መንገድ እንዳያጣ ነው አጐቱን ግደሉት ያለው” ብለዋል፡፡ ሆኖም የአላህ ፈቃድ ሆኖ አቶ በድሩ ተደብድቦ ሲተርፍ፣ ኢ/ር ጀሚል ለሞት በቃ ብለዋል፡፡
“ወንጀሉን ፈፃሚውም ሟቹም ቤተሰቤ ነው ያለው ሌላ የቡታጅራ ከተማ ወጣት ነዋሪ፤ አጐቱ በድሩ ሱልጣን የሊቃን ስርዓት ከማክበር ባሻገር ከቃጥባሬ እስከ ወልቂጤ ያለ 12 ኪ.ሜ ኮረኮንች መንገድ በአስፋልት ለመቀየር አስቦ፣ ሟችን ጨምሮ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎችን ከአዲስ አበባ ይዞ እንደሚመጣና መንገዱን በተመለከተም ከህዝቡ ጋር ምክክር ለማድረግ ቀጠሮ አስይዞ እንደነበር ወጣቱ ይናገራል፡፡ “እወጃውን በግንቦት 19 አውጆ፣ ለበዓሉ ቀረ፤ ከዛን በፊት ቀርቶ አያውቅም” የሚለው ወጣቱ እነዚህ ሰዎች አገር ሰላም ብለው ሁለት ሚኒባስና አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ይዘው ግንቦት 20 ቀን 2004 በስፍራው መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ “በዋና ገዳይነት ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኘውታናሽ ወንድሙ ነሲቡ ሱልጣን “የተባሉት ሰዎች መጥተዋል ተነሱ” በሚል ድብደባውን መጀመሩንና ከሞቱት ግለሰብ ውጭ 19 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ወጣቱ ገልጿል።
የገዳይ የቅርብ ዘመድ እንደሆኑ የነገሩን ሌላው አዛውንት የአካባቢው ነዋሪ፤ ወንጀለኛው በእናቱ በኩል ዘመዳቸው እንደሆነ ገልፀው፤ “አንድ ጊዜ ወፍጮ ቤትህ በደንብ እንዲሰራ፣ ንግድህ እንዲቃና ከሱዳን ያስመጣሁት አዋቂ ስላለ 30 ሺህ ብር ከፍለህ መድሀኒት ላሰራልህ ብሎኝ እምቢ ብየዋለሁ” ብለዋል፡፡ ወንጀለኛው ጥንቆላ ውስጥ መግባቱንና ህዝቡን እያንቀጠቀጠ ገንዘብ እንደሚቀበልም ነዋሪው ተናግረዋል፡፡
የቡታጅራና አካባቢው ነዋሪዎች በእስር ላይ ስለሚገኘው ፍርደኛ፤ ሲናገሩ “እስር ቤቱ ለእርሱ መዝናኛው ነው፤ ድንኳን ተጥሎለት አሁንም ከህዝቡ ገንዘብ እየሰበሰበ ነው፤ ከእስር ቤት እየወጣ በየጊዜው ወደ ቤቱ ይሄዳል፣ “ወራ” የተባለውን የራሱን ሀይማኖታዊ ስርዓት ከማረሚያ ቤት ወጥቶ እቤቱ ነው ያከበረው፤ እርሻውን 50 ኪ.ሎ ሜትር እየሄደ ያሰራል፤ በየጊዜው ከማረሚያ ቤቱ 18 ኪ.ሜትር ወደሚርቀው ቤቱ ይሄዳል፤ ከፍተኛ ሀዘንና ችግር ቢከሰት እንኳን ከማረሚያ ቤቱ ሰባት ኪሎ ሜትር ራዲየስ መራቅ በህጉ አይፈቀድም፤ ለዚህ ሰው ሽፋን የሚሰጥበት ሁኔታ ለአካባቢው ስጋት ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡
“ከፖሊስ ጣቢያ በህገ-ወጥ መንገድ ነው ያመጣነው”
ኮማንደር ወንደሰን አበበ
የቡታጅራ ማረሚያ ተቋም ሀላፊ ኮማንደር አበበን በማረሚያ ተቋሙ ተገኝተን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ “በ2004 በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰው የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ሰዎች አሉ” በማለት ነው ጥያቄያችንን መመለስ የጀመሩት፡፡ በነፍስ ግድያው ወደ ማረሚያ ቤት የመጡት 19 ሰዎች እንደነበሩ ጠቁመው 14ቱ በአመክሮ እንደተፈቱ ኮማንደሩ ገልፀዋል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ካሉት መካከል አንዳንዶቹ እንደፈለጉት እየወጡ ይገባሉ የሚባለውን በተመለከተ ሲናገሩም፤ “የህግ ታራሚዎች ገና ወደ ማረሚያ ቤት እንደገቡ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች እንዳሉባቸው ይናገራሉ” የሚሉት የተቋሙ ሀላፊ፣ ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ ቤተሰባቸውን ሳያረጋጉ፣ ማረሚያ ቤት እንደሚገቡ ጠቅሰው፤ ከዚህ አንፃር ህጉ ፈቃድ ይሰጣቸዋል ይላሉ፡፡ “ይህ ማለት ግን በየቀኑ ይወጣሉ ማለት አይደለም” ያሉት ኮማንደሩ፤ “በርካታ ንብረት በትኜ ነው የመጣሁት” የሚል ማመልከቻ ካቀረቡ በኋላ ጉዳዩ ተጣርቶ አጃቢ ተመድቦላቸው ሄደው እንደሚመጡ፣ ይህን የሚፈቅድ ህግ እንዳለም አብራርተዋል፡፡ ከኢ/ር ጀሚል ግድያ ጋር በተያያዘ በተቋሙ በእርምት ላይ የሚገኙት ሰልማን ሰይድ የአያያዝ አግባብ ሲያስረዱም፤ ሰውየው የልብ ህመም ስላለባቸው በየሶስት ወሩ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ እንደሚመላለሱ ገልፀው፣ ይህ የሀኪም ትዕዛዝ እና የጤና ጉዳይ ስለሆነ የግድ መሄድና መታከም እንዳለባቸው፤ ምንም ማድረግም እንደማይቻል ኮማንደሩ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
“የሰልማን ሰይድ ፋሪስን ጉዳይ በተመለከተ ውጭ ይወጣሉ በሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ይቀርብልናል” ያሉት ኮማንደር ወንድወሰን፤ ይህንንም በትክክለኛው መንገድ እየመለሱ እንደሚገኙ፣ ጤንነታቸውን በተመለከተና የመኝታን ጉዳይም ጭምር ዶክተሮች በሰጡት መመሪያ መሰረት ለብቻቸው እንዲተኙ መደረጉን ያብራራሉ፡፡
ለሰልማን ሰይድ ከህጉ ውጭ የተለየ ነገር አልተፈቀደለትም ይላሉ የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ፤ አንድ የህግ ታራሚ ወላጆቹና ቤተሰቦቹ ቢሞቱበት 6 ኪ.ሜ ራዲየስ ድረስ ሄዶ እንዲቀብር የማረሚያ ቤቱ አሰራር ይፈቅዳል ያሉት ኮማንደሩ፤ ቡታጅራ ሆስፒታል የተኛ የቅርብ ቤተሰብ (ዘመድ) ካለውም ጠይቆ እንዲመጣ ፈቃድ እንዲሰጥ ህጉ ያዛል ብለዋል፡፡ “እርግጥ ሰልማን ሰይድ ፋሪስ በአንድ ወቅት እህል መሰብሰብ አለብኝ፣ ገንዘብ ያለበትንም ለባለቤቴ ልንገር ብለውን ፈቅደንላቸው ሄደው መጥተዋል፤ ከዚህ የዘለለ ግን እንደ ውሀ ቀጂ የሚመላለሱበት ጉዳይና የተለየ እድል የሚሰጥበት የህግ አግባብ የለም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኦሮሚያ ክልል ሄደው ማሳ ያሰራሉ፣ “ወራ” የተባለውን የራሳቸውን የሀይማኖት በዓል በቤታቸው ያከብራሉ፤ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ዳስ ተጥሎ ገንዘብ ይሰበስባሉ በሚል በታራሚው ላይ የሰማነውን መረጃ የጠቀስንላቸው ኮማንደሩ ሲመልሱ፣ “ኦሮሚያ ድረስ የሚሄዱበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም በነፍስ ግድያ የገቡ ሰው ናቸው በቀል ስለሚኖር በሰው ጉዳት ሊደርስባቸውም ጉዳት ሊያደርሱም ይችላሉ በሚል የማረሚያ ተቋሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ሌላ ታራሚ፤ ገንዘቤን ልሰብስብ፤ ቤተሰቤን ላረጋጋ ቢል ይፈቀድለት እንደሆነ ጠይቀ ናቸውም፤ ድንገት ተይዞ ለገባ ታራሚ ህጉ ለአንድ ቀን ብቻ እንደሚፈቀድ ተናግረዋል፡፡
ዳስ ተጥሎላቸው ገንዘብ ይሰበስባሉ የሚለውን በተመለከተም፤ እኔ በማረሚያ ተቋሙ ስሰራ 11 ዓመቴ ነው፤ በዚህ አመት ውስጥ በቀን ብዙ ጠያቂ መጣ ከተባለ 10 ወይም 15 ሰው ነው” ያሉት ሃላፊው፤ እኚህ ሰው ወደማረሚያ ቤቱ ከመጡ በኋላ በቀን ከ100 እስከ 250 ሰው ወደማረሚያ ቤቱ መምጣት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ የታራሚ መጠየቂያም በጣም ጠባብ በመሆኑ የግድ ዳሱ መጣል ስለነበረበት በላስቲክ ዳስ ተሰርቶ እንዲጠየቁ መደረጉን ገልፀው፤ “ይህንን ያደረግነው የሌሎች ታራሚዎችን ጠያቂዎች እድል ላለመንፈግ ነው” ያሉት ኮማንደሩ፤ ሰውየው ገንዘብ ይሰብስቡ አይሰብስቡ ማረሚያ ተቋሙን አይመለከተውም ብለዋል፡፡ ጠያቂው ከጠየቀ በኋላ ገንዘብ ሰጥቷቸው እንደሚሄድ በመግለጽ። “ከዚህ በተረፈ ከሌሎች ታራሚዎች የተለየ እድልና ቅድሚያ ለእርሳቸው የምንሰጥበት ምክንያት የለም፤ ዳሱንም ቢሆን ተቋሙ ሳይሆን ራሳቸው ታራሚው ናቸው ያዘጋጁት፡፡” ብለዋል፡፡ (በነገራችን ላይ በሰማያዊ ላስቲክ የተጣለውን ዳስና የተነጠፈውን ጂባ ምንጣፍ በስፍራው ተመልክተናል፡፡)
“እንኳን የተለየ እድል ልንሰጣቸው ከፖሊስ ጣቢያም ያመጣናቸው በህገ ወጥ መንገድ ነው” ያሉት ኮማንደሩ፤ ግድያው ራሱ የተፈፀመው በሃይማኖቱ የተነሳ መሆኑን፣ ሟችም አደጋው የደረሰባቸው በሰው ማመን የለብንም በሚል መሆኑ እንደሚታወቅ ገልፀው፣ “ታራሚው ከአያቴ፤ ከአባቴ የወረስኩት ነው የሚለውን እምነት እንዲያራምድ እንዴት ወደቤቱ እንልከዋለን” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እንደውም ከታራሚው ጋር የተፈጠረ ግጭት እንደነበር የሚያስታውሱት ሃላፊው፤ በአንድ ወቅት በማረሚያ ተቋሙ ውስጥ ከብት ሲታረድ “ሼኩ ያረዱትን ሳይሆን እራሳችን ያረድነውን ነው የምንበላው” በሚል ከታራሚው ጋር በነፍስ ግድያው ተፈርዶባቸው የመጡት ችግር ፈጥረው እንደነበረና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቄራ እየታረደ ስጋ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ታራሚው ከዚህ በፊት በሰዎች ላይ ሽጉጥ ስለመተኮሳቸው፣ ብዙ ጊዜ ስለመከሰሳቸውና በማረሚያና በፖሊስ ጣቢያ ሽፋን ይሰጣቸዋል ስለመባሉ ያውቁ እንደሆነ ጠይቀናቸው፤ ሰውየው ወደማረሚያ ቤቱ የገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ጠቅሰው ቀደም ሲል፣ ፖሊስ ጣቢያ ገብተው ይሆናል እንጂ ማረሚያ ቤት አልመጡም ብለዋል፡፡ “እርግጥ እኛም ከፖሊሶች እኒህን ታራሚና ሌሎች 19 ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ነው የተቀበልናቸው ያልኩሽም፤ ገና ሳይፈረድባቸው ፖሊስ ጣቢያ እያሉ ሰዎችን ማነሳሳትና መሰል ድርጊቶችን ይፈጽሙ ስለነበር፣ ነገሩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይዞር በመፍራት ነው ፍርድ ከማግኘታቸው በፊት ያመጣናቸው” ብለዋል፡፡
ድሮ አሜሪካም ሆኜ እዚህም ከመጣሁ ጀምሮ ሰልማንና ወንድሞቹ የሚያራምዱት እምነት አይስማማኝም ነበረ “የግድያው መንስኤም ይሄው ይመስለኛል” የሚሉት አቶ በድሩ፣ የጀሚል ሞት ግን የእድሜ ልክ ሀዘን እንደሆነባቸው በሀዘን ገልፀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ ነፍሰ ገዳዮቹንና ግብረአበሮቻቸውን በይግባኙ የቀነሰላቸው የእስራት ጊዜና 14 ሰው በነፃ የለቀቀበት መንገድ ለኢ/ር ጀሚል እና ለቤተሰቦቹ፤ ለእኛም ጭምር ሁለተኛ ሞት ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ለሰበር ሰሚ ይግባኝ ቢጠይቅም ይግባኙ የዘገየ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ፋጡማ፤ ወደ ሰበር ችሎት ጉዳዩ ከመጣ በኋላ 14ቱን ሰዎች ያስቀርባቸዋል በሚል ሰበር ችሎቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ትዕዛዝ ቢሰጥም የተፈቱት 14 ሰዎች ግን ራሳቸውን በመሰወራቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ ገልፀውልናል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለሶስተኛ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለጥቅምት 26 ቀን 2006 ሰዎቹ እንዲቀርቡ ያዘዘ ሲሆን በቀጠሮው ቀን ይቅረቡ አይቅረቡ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል – የሟች ባለቤት ወ/ሮ ፋጡማ፡፡
የ58 አመት ጐልማሳ የነበሩት ኢ/ር ጀሚል ሃሰን፤ ኪናንጀሚልና ኢፕቲሀጅ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ከኮሜርስ በአካውንቲንግ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ትምህርት መማራቸውንም ባለቤታቸው ወ/ሮ ፋጡማ ተናግረዋል፡፡ ከረጅም ዓመት በፊት “ርብቃ” የተባለ መጽሐፍ የተረጐሙ ሲሆን መታሰቢያነቱንም ለገዳይ አያት ሻለቃ ሱልጣን እንዳደረጉ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስድስት ያልታተሙ የትርጉም ስራዎች እንዳሏቸውና በመጨረሻው የእድሜ ዘመናቸው አካባቢ “the three Cup of Tea” የተሰኘ መጽሐፍ ተርጉመው ለህትመት ሲያዘጋጁ እንደነበር ባለቤታቸው ተናግረዋል፡፡ “አፒክስ” የተሰኘ የጉዞ ወኪል ድርጅት የነበራቸው ኢ/ር ጀሚል፤ “ኦፕቲፋም” የተሰኘ የኔትወርክ ቢዝነሳቸውን በማናጀርነት ይመሩም እንደነበር ታውቋል፡፡
ኢ/ር ጀሚል ከመሞታቸው በፊት “ሁሉንም ሰው ይቅር ብያለሁ፤ ገዳዮቼንም ጭምር” የሚል ቃል መናገራቸውን፣ ተጨማሪ መልዕክት ለማስተላለፍ እስኪርቢቶ ጠይቀው መፃፍ እንደተሳናቸው ባለቤታቸው በእንባ ታጅበው ነግረውናል፡፡ “ይህን ጉዳይ አይቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ፤ ልጆቼም እኔም ፍትህ እንሻለን” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

http://www.addisadmassnews.com

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s