ስቅለትና ትንሣዔ ወያኔና ኢትዮጵያ (ዳኛቸው ቢያድግልኝ)

ለክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ እንኳን ለብርሀነ ትንሣዔው አደረሳችሁ። የስግደትን ክቡርነት፣ የይቅር በለን የንስሀ ጸሎትን ታላቅነት በማክበር ለአመት ከዘለቀው የድምጻችን ይሰማ ትግል ጋብ ብላችሁ ለጸሎታችን ይሰማ ክብር ለሰጣችሁ እግዚአብሄር ያክብራችሁ። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መሆኑን ስላስተማራችሁ የተመሰገናችሁ ሁኑ። በፍቅር እንደምንከብር በነጻነትም እንደምናድግ ከዚህ በላይ ትምህርትስ እንደምን ይገኛል? መሪውን የሚያስተምር፣ ከመሪዎቹ ቀድሞ ከፊት የሚገኝ ሕዝብስ እንደ ኢትዮጵያውያን ያለ ወዴት አለ?

አይሁዶች የአብራካቸው ክፋይ ኢየሱስን የማርያምን ልጅ ለመስቀል አላመነቱም። ፍርድ ሰጪው ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ እጆቹን ታጠበ። እየወገሩ የሰቀሉት ግን ሀሴትን አገኙ። ሟቹ ከመስቀሉ ላይ ሆኖ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው እያለ ወደ አባቱ ጮኸ። እየጮኸም ምህረትን እየለመነም ህይወትን ለመሰናበት ከመስቀሉ ላይ ተቸንክሮ የፀሀይን ብርታት የሰውን ጭካኔ እየተመለከተ አዘነ። ዛሬ ላይ ቆመን ስንመለከት ግን እግዜር ካልጠፋ ነገር ለሰው ልጅ ምህረት ማድረግ ነበረበት ወይ? ያሰኛል። በዚህች ምድር ውስጥ እግዜር ከፈጠረው መካከል እንደሰው ልጅ ክፉ እንደሰው ልጅ አጥፊ ነበርና ነው ወይ የሚምረን? ማለት ፌዘኛነት አይደለም። በዚህች ምድር ላይ የራሱን ዘር ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚያደባና የመሳርያ አይነት የሚፈብርክ ቢኖር ‘ሆሞ ሳፒየንስ’ ነኝ ብሎ ራሱን የጠራው የሰው ዘር ብቻ ነው። ወይም ከአዳምና ከሄዋን መጣን ብሎ የሚያምነውና እግዜር በአምሳሉ ሰራኝ የሚለው ፍጡር ብቻ ነው። እናም በሰንበት ቀን በመስራቱ፣ የታወረን ብርሀኑን ስለሰጠው ኢየሱስን የራሱ ወገኖች በጎልጎታ ላይ ቸነከሩት።

ይኸው ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ መሰቀያዋ እየተገረፈች እየተነዳች ነው። ቀሚስዋ ብጥስጥሱ ወጥቷል። ያጠቡና ያሳደጉ ጡቶችዋ በመንጠቆ እየተጎተቱ ነው። ፀጉርዋ ተገምዶ ቁልቁል ወርዷል፣ አይኖችዋ ጎድጉደዋል። በጭኖችዋ ላይ ደም እየተንዠረገገ ይወርዳል። እናም ወደሞትዋ እየተነዳች ነው። አሞራዎች ጣዕረ ሞትን አጅበው የሚመጡ ይመስል ሰማዩን ክብ ሰርተው ይከንፉበታል። ጅቦቹም እንዲሁ ዙርያውን አስፍስፈዋል። ከጉልበተኞች የተረፈውን ለመቀራመት ተኩላና ቀበሮ ቦታ ቦታ ይዘዋል። የትግሬ ጎጠኞች እንደ እሾህ አክሊል አናትዋ ላይ ሆነው ይጠቀጥቋታል። ጀሌዎቻቸውን እያዘዙ ጎንዋን፣ እግርዋን፣ ሽንጥዋን መላ አካልዋን በጦር ይሸቀሽቃሉ።  ዘርፈው የያዙትን ወርቅ በከረጢት ጀርባቸው ላይ አንጠልጥለው፣ ሚስቶቻቸውም ቁልል ሹሩባቸው ላይ ወርቁን ገምደው ከበሮ እየደለቁ ትሰቀል! ትሰቀል! እያሉ ይጮሃሉ።   እኒህ ገራፊዎች በእቅፍዋ የነበሩ ልጆችዋ ጡትዋን ጠግበው እሸትዋን በልተው ሀ..ሁን ቆጥረው ያደጉቱ ግን ክህደት፣ እብሪትና ጎጠኛነት እንደ አደንዛዥ እፅ ያሰከሩዋቸው፣ ያንቀዠቀዣቸው ክፉ ፍሬዎችዋ ናቸው። ኢትዮጵያ ሆኖ የማይታወቅ ክህደት፣ ተደርጎ የማያውቅ በደልን የምትሸከመው ልጆቼ ባለቻቸው የሰው አሜኬላዎች መሆኑ ይሆንዋል እጆችዋን ወደ ፈጣሪዋ እንድትዘረጋ የሚያደርጋት።  የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የምትል ይመስላል። አዎ የሚሰሩትን ቢያውቁ አጥፍተው ለመጥፋት ባልተጣደፉ ነበር። እንኳን ኢትዮጵያ እኛም ትቢያዎቹ የሚሰሩትን አያውቁምና በአዋቂዎች ይተኩ የምንለው ለዚሁ ነው።

ትንሣዔ መኖሩን ቢያውቁ ሰቃዮች ለመግደል ባልቸኮሉ ነበር። ትንሣዔ መኖሩን ቢያውቁ ራስህን አድን እያሉ በኢየሱስ ላይ አያሾፉም ነበር። ኢትዮጵያም ከወደቀችበት ቀና እንደምትል፣ ኢትዮጵያም ጎጠኞችና ሆዳሞችን አሽቀንጥራ ጥላ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና እናም ትንሳዔዋ እውን እንደሚሆን ቢያውቁ እፍኝ የማይሞላ ወርቅ አያሳሳቸውም ነበር። እነርሱ የታሪክ ቅጽበቶች፣ እየጠፉ ያሉ ሻማዎች መሆናቸውን ቢያውቁ ኖሮ በህይወት እያሉ፣ ብርሀናቸው ሳይጠፋ ንስሀ በገቡ፣ ምህረትን በጠየቁ ነበር። ግን ለዚህ አልታደሉምና ስቀላት ስቀላት እያሉ እየጮሁ ነው። ኢትዮጵያ እጆችዋ ግራና ቀኝ ተለጥጠው የማኅጸንዋ ፍሬዎች ሲያጠፏት እየተመለከተች ነው። የእናት ነገር ሆኖባት አሁንም የሚሰሩትን አያውቁምና… ትላለች።

የኢትዮጵያ ቆነጃጅት፣ እሸትና እምቡጦቹ የነገዎቹ እናቶች፣ የነገዎቹ ሚስቶች አገር አጥተው፣ ጠባቂና ተንከባካቢ ጠፍቶ፣ በባርያ ፈንጋይ የትግሬ ገዢዎች ይሁንታ በትግሬ ነጋዴዎችና ደላላዎቻቸው ለገበያ ቀርበው እየተቸበቸቡ ነው። የማንም ዝተታም አረብ፣ ጋጠወጡና ባለጌው በኒህ ሕጻናቶችና ወጣቶች ላይ ቅንዝረኛ ገላውን ያሳርፋል። ያቆሽሻቸዋል ያረክሳቸዋልም። በወር አንድ መቶ ዶላር ለማግኘት አንድ መቶ ጊዜ ይዋረዳሉ፣ አንድ መቶ ጊዜ ይገረፋሉ። እንዲያም ሆኖ የለፉበትን እንኳን ሳያገኙ አብደው ይመለሳሉ ወይም ራሳቸውን ያጠፋሉ። ባይሞቱም ሞተናል ተዋርደናል ረክሰናል ብለው የሚያምኑ ይሆናሉ። አዎን ኢትዮጵያ በልጆችዋ ክፋት ወደ ሞት እየተነዳች ነው። የትግሬ ጎጠኞች ቅንጣት ታክል አያመነቱም። ጥላቻና ንቀታቸው ጥግ ደርሷል። አረቦች ወይም ሌሎች ወጣቶችን የሚመለከቱት በግ ተራ እንደወረደ ሸማች ነው። ኩላሊት አላቸው፣ ልብ አላቸው፣ አይናቸው ያምራል ምርጥ መለዋወጫዎች እያሉ ያዩዋቸዋል። የሰው ቅርጫ ሊያደርጉዋቸው አሰፍስፈው ይጠብቃሉ። የአማራ፣ የኦሮሞና የሌላው የጠላት ልጆች ናቸውና ጎጠኞች እብሪትና አሸናፊነት በተሞላው ፌዝ ገንዘባቸውን እየቆጠሩ ወላጅ እናታቸውን መስቀል ላይ ቸንክረው ትሰቀል! ትሰቀል! ይላሉ።

የኢትዮጵያ ህጻናት ወላጅ አልባና ችግረኛ ወላጆች ያሉዋቸውም ጭምር እየተለቀሙ በግላጭ እየተሸጡ ነው። ገበያውን ያደሩትና በንግዱ የከበሩት ባለ ንግድ ፈቃዶቹ፣ ሻጮቹና አሻሻጮቹ ወይም ጎጠኞቹ አለዚያም ከነርሱ የተጠጉቱ ሆዳሞች ናቸው። ምንኛ ጭካኔ ምንኛ ክፋትስ ነው ይህንን የሚያስፈጽም ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ከተሸጡት ህጻናት ውስጥ ራሳቸውን የገደሉ፣ አእምሮአቸው የታወከና ሌላም በደል የደረሰባቸውን ቤቱ ይቁጠረው። የህጻናት ፖርኖግራፊና፣ የዝሙት ባርያ የሆኑ ውብ ወጣት ሴቶች ብዛትን ኢትዮጵያ በቅርቡ ሬከርድ ትበጥስ ይሆናል። እነዚህ ለባርነት የተጣሉ ህጻናት እንባ እንደ ጅረት ይፈሳል። በዚያ ጨቅላ እድሜ አምሳያቸው የሌሉበት የራሳቸው የቆዳ ቀለም ግራ የሚገባቸው እርዳታ ፍለጋ የሚቁለጨለጩ አይኖች የሚፈልጉት ሀብታም እናትና ብዙ አሻንጉሊት ሳይሆን ወላጅ እናትና አባታቸውን ወንድም እህቶቻቸውን ነው።  ይህንን ፍቅር የሚነፍጉና ህፃናትን እንደ ድንች ደርድረው የሚሸጡ ነጋዴዎች ተዘቅዝቀው ቢሰቀሉና ከስራቸው እሳት ቢነድም እንኳ የሚበቃቸውን ያህል ቅጣት የሚያገኙ አይመስለኝም።  ያደኸያቸው ስርዐት መጠየቁ ቀርቶ የግፍ ግፍ በፎጣ ተጠቅልለው እንደ ቅርጻ ቅርጽ የውሸት ስም፣ የውሸት ታሪክ ተሰርቶላቸው ይሸጣሉ። ህፃናቱ በመላው ዓለም ተበትነው የሚደርስላቸው ወገን አጥተው ከንቱ ጩኸት ያሰማሉ። የጣር ጩኸታቸውን የደስታ ዘፈን አድርገው የሚጨፍሩት ጨካኞች አገራቸውን እናታቸውንን ከተራራው አውጥተው ሥጋዋን ሊቃረጡ ትሰቀል ትሰቀል ይላሉ ከበሮ እየመቱ። ትሰቀል! ትሰቀል!

ጠላት ሲመጣ ጓዜን ጨርቄን የማይለውና በባዶ እግሩ ጦሩን እየሰበቀ ዳር ከዳር ይዘምት የነበረው ገበሬ። ዳገት እየቧጠጠ ግን በኢትዮጵያዊ ኩራቱና በእምነቱ ጸንቶ የኖረን የህብረተሰብ ክፍል አማራ ነህና አገርህ አይደለም ተብሎ አገር ባቀና ደሙን ባፈሰሰ፣ በረሀብ በተቆላ፣ የውሸት የገዢ ስም ለጥፈው፣ ኢትዮጵያዊነቱን ተጠይፈው፣ ለነጻነት ቀናዒ መሆኑን አውግዘው እያሳደዱ ባለሀገሩን አገር አልባ ያደርጉታል። በትግራይ ጎጠኞች አስጨፍጫፊነት ቀሳውስቱን ከደብር፣ ገበሬውን ከኖረበት መንደር፣ እያፈናቃሉ ለሀገሩና ለባንዲራው ክብር በመሞቱ ይጨፈጭፉታል። ያቺን አገር ያቺን እናት የሆነችንን አገር ከጠላት መንጋጋ ያወጡት ለጠላት እየተሰጡ የሚጠሉዋትን ኢትዮጵያ ደግሞ ጎጠኞቹ ትሰቀል! ትሰቀል እያሉ ይጮሃሉ።

የሚያድኗት ልጆች ካሉ፣ ጣርዋና ጩኸትዋን ሰምተው ከህልፈትዋ በፊት የሚደርሱላት ጀግኖች ካሉ፣ ከራሳቸው ቅንጣቢ የእድሜ ዘመንና የስልጣን ጥም በላይ በሞታቸው ህይወትን፣ የሚሰጡ ልጆች ካሉ ለኢትዮጵያም ትንሳዔ ይኖራታል። የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ካለ ይላል መጽሀፉ….  ያለ ጥርጥር ከዚያም የገዘፈ እምነት አለን የተጋረጠውን ክፋት የሚገፋ ።

የሀገራችን ኢትዮጵያ ትንሣዔም ቅርብ እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳን።

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/7552

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s