ሕወሃት- አድሮ ጥጃ (ይኸነው አንተሁነኝ)

እንደ ሀገራችን ወግና ባህል እንደ እድሜ ጠገቦቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን ትውፊት ስለራስ ስራና ታታሪነት ሌሎች ሰዎች ሲናገሩልን እንጅ እኛው ስንለፈልፈው አያምርም፤ ለዚያውም የተደረገ የተከወነ ታሪክ ከሆነ ማለቴ ነው። ከዚያም ሲያልፍ ስራችን እራሱ ስለሚናገር የኛን የራሳችንን ምስክርነት አይፈልግም። እንዲያ ካደረግን ግን ጉረኛ ከማስባሉም በተጨማሪ በራስ ብቻ መታበይን ሊፈጥር ይችላልና ነው። እንግዲህ ቀደም ብየ እንዳልኩት ይህ ሁሉ በእርግጥ የከወነው ስራ ካለ ማለት ነው። ይሁን እንጅ አንዳንድ ሰዎች ከወግ ባህላችንና ከእድሜ እኩዮቻቸውም እረ ከታናናሾቻቸው ስርአትም ባፈነገጠ መልኩ ሲዘባርቁ ይታያሉ። የሰው ማንነቱ በማይታወቅበት ስራው በማይነገርበት የቀን ተቀን እንቅስቃሴው በማይታይበት ሀገር ቢሆን ያሻውን ቢያወራ እንዲህም እንዲያም ነኝ ቢል አይታወቅምና ቢያንስ እስኪታወቅ በመጠኑም ቢሆን ተቀባይነት ሊያገኝ በቻለ ነበር። እንደ ፀሐይ በጠራ ብርሃን በሚነበብበት ሀገር ሲነገር ግን ያስተዛዝባል ያስተቻል ያቀላል ያዋርዳልም በተለይ የቀረ ያልተዋረደ ክብር ያልቀለለ ማንነት ላለው ማለቴ ነው።

የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሆነ መሽከርከሪያ የህወሃት የጥፋት መሃንዲስ የሚባልለት ተነጋጋሪውና አነጋጋሪው ሽማግሌው ስብሃት ነጋ ባንድ አታካች ንግግሩ “ሕወሃት ኢሕአዴግን የመሰለ ፓርቲ በአፍሪካ የለም” ብሎ የተናገረው ነው። መቼም እኔም ካልተሳሳትኩ ይህ ንግግር ለኢትዮጵያዊያን የተነገረ ነው። ሕወሃት ኢሕአዴግን ግጥም አድርገን ለምናውቅ፣ ማስረጃ ማቅረብ ቢያስፈልግ እስከ አገጭ ጢም አድርን ለምናቀርብ ኢትኦጵያዊያን፣ ታሪኩን መዘርዘር ቢያስፈልግ ከምስረታው እስካለንበት ድረስ የከወናቸውን ድርጊቶች ከቦታና ጊዜ ጋር አቀናጅተን ለምናቀርብ ዜጎች መነገሩን ስናስታውስ እውነትም  “ባለጌ አፉን እንጅ እግሩን አያድጠውም” የሚባለውን እናረጋግጣለን።

በነገራችን ላይ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንደሚባለው በተለያዩ ስሞች ተሽሞንሙኖ የሚጠራው አንዱና ብቸኛው ሕወሃት ብቻ ነው። ኢሕአዴግ፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድም ሆነ ደሕዴን አጋር የሚባሉትም ቢሆኑ ሁሉም የሚመሩት በሕወሃት ነውና። ስለዚህም በመላ ሀገሪቱ ሕወሃት ያዛል ሕወሃት ይፈጽማል። ይህ ነው መሬት ላይ ያለው ነባራዊው እውነት። ስለሆነም ስብሃት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ሕወሃትን በመከላከል ላይ ባመዘነው ንግግሩ የዘላበደውም ስለ ሕወሃት ብቻ ነው። ግን ሕወሃት ማነው? በእርግጥ ከሀገር ተሻግሮስ በአፍሪካ ደረጃ የሚያወዳድር ማንነት አለው? ሕወሃት ሕዝባዊስ ሊባል ይችላል?

ካመሰራረቱ እንኳ ብንጀምር ሕወሃት ስብሃት እንደሚናገርለት ከሀገር አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የሚወራለት አይነት አልነበረም። ሕወሃት በተመሰረተባቸው ዓመታት በመላው አፍሪካ የሶሻሊዝም አይዲዎሎጂ በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ነበር። የሀገራችን የጊዜው ወጣቶችና ምሁራንም ይህንኑ የዘመኑ ወረርሽኝ በመከተል በመጠኑ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው ነገር ግን በመርህ ደረጃ ከሶሻሊዝም አስተምህሮ ያልወጡ ፓርቲዎችን አቋቁመው የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነበር። የተለያዩ ግልጽ ወይም ሕቡዕ መንገዶችን በመከተልም ሕዝባዊነታቸውንና አብዮታዊነታቸውን እንዲሁም ሀገራዊ ራዕያቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳውቁበት ወቅት ነበር። ሕወሃት ግን ከአፍሪካ ይቅርና በኢትዮጵያ ካሉ ፓርቲዎች እጅግ ባፈነገጠና ባቅራቢያው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም በጣም በተለየ መልኩ ገና ከምስረታው ጀምሮ ልዩነትን፣ ጎተኝነትን፣ ጠባብነትን በጥቅሉ እናንተ እና እኛ የሚልን አመለካከት መሰረት አድርጎ የተቋቋመ መሆኑ ሲታወስ ስብሃት ነጋ “ስመሰክርልህ ስመሰክርልህ ዋልኩ ቢለው እኔም ስታዘብህ ስታዘብህ ዋልኩ አለው” የሚባለውን ብሂል ያስታውሰናል። ባሁኑ ሰአትም ሕወሃት ኢሕአዴግ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ የተወገደውን የአፓርታይድ ስርአት በሀገራችን ለመመስረት በመለማመድ ላይ ይገኛል እንጅ ለመወዳደርስ በአፍሪካ ደረጃ ይቅርና ለሀገር ውስጥም ብቁ አይደለም።

ምናልባት ስብሃት የሚያወራው ስለ ሕወሃት ኢሕአዴግ ክፉ ስራ ከሆነ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም ደረጃ ለንጽጽር ቢቀርብ ተቃውሞ የለንም ትክክልም ነው። ምክንያቱም እየመራሁት ነው ከሚለውና የራሴ ከሚለው ሕዝብ ይልቅ ለሌሎች አገሮች ሕዝቦች አብዝቶ የሚጨነቅ፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን  የሞቱለትንና የደሙለትን የሀገራችንን መሬት ቆርሶ በግልጽ ለማይታወቅ  የሰላም ሃሳብ ለሌሎች የሚሸልም፤ ባለ ሀገሩን ባለ መሬቱን በግዳጅ እያፈናቀለና እያሰደደ መሬቱን ለሌሎች ዜጎች የሚሸጥ በእርግጥ ከሕወሃት ኢሕአዴግ በቀር በአፍሪካ ቀርቶ በዓለም ሌላ ፓርቲ ሊገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ አይቻልምና ነው።

ሽዎችን በማርገፍና ሚሊዮኖችን በማሰደድ የሚታወቀው ርሃብ ሀገራችንን ሰቅዞ በያዘበት ወቅት ለትግራይ ክልል እንዲያከፋፍል ከዓለም ዙሪያ የተላከለትን ፈጥኖ ደራሽ የገንዘብና የእሕል ርዳታ በእርግጥ ወደ ራሱ የግል ኪስ የከተተና ባስር ሽዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን ሞት ምክንያት የሆነው ማነው? ሕወሃት አልነበረምን? ታዲያ ይህ ጎጠኛ ድርጅትስ ለንጽጽር መቅረብስ ነበረበት? “ስራ ያጣ ገንፎ ያላምጣል” ሆኖበት ነው እንጅ  እውነታውንማ ከስብሃት የተሻለ ማን ሊያውቅ ይችላል?

ሕወሃት በሽፍትነትና ባሸባሪነት ዘመኑ ወቅት በትግራይ ሕዝብ የደረሰበትን መገለልና መጠላት እንዲሁም ያጋጠመውን የታጋይ ችግር አንደገና ለመመለስ በማሰብ በተቀነባበረ ሴራ የሀውዜንን ሕዝብ ለእርድ በመሰዊያው ላይ ያቀረበ እጅግ ጨካኝ ጎጠኛ ቡድን ነው?  በመጠኑም ቢሆን የምርጫ ነጻነት በተሰጠው የ1997 ዓ/ም የሀገር ውስጥ የምረጡኝ ውድድር ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምጹ የቀጣውን ሕወሃትን “ሜዳ መራመድ ሳታውቅ መሰላል መውጣት ማን አስተማራት?” እንዲሉ ስብሃት ደግሞ እጅግ አዘልሎ ከአፍሪካ ሊያነጻጽረውና ሲከፋም መሪ ሊያደርገው ይከጅላል።

የፓርቲነትም ሆነ የመንግስትነት ቅርጽ የዣለሁ የሚለው ሕወሃት ያጎራባች ሀገሮች መንግስታት ከሚያደርጉት በጣም ትንሹን ለመከወን እንኳ አልቻለም። አሁን በቅርቡ መንግስት ካቆመችው ሶማሊያ እንኳ እጅግ በከፋ መልኩ የጋዜጠኞችን መብት የሚረግጥ የሚያስርና የሚያሰድድ የግል ራዲዮኖችም እንዳይኖሩ ቀን ከሌት የሚሰራ፤ ጋዜጦች እንዳይታተሙና እንዳይሰራጩ የሚያግድ፤ ብቻውን እየተወዳደረ እንኳ (ብቻን መወዳደር ለሕወሃት የተለመደ ነው) ምርጫን በማጭበርበር ኮሮጆን እንዳለ በመስረቅና በመተካት ጭምር የተካነ በእርግጥ ከሕወሃት በቀር ማን አለ? ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ቢወዳደር።

የሕወሃት የክፋት አባት የሚባለው ስብሃት እራሱ እየከሰሰ ራሱ እየፈረደ ስንቶቹን የሀገር ተስፋዎች በልቷል። እሱና እሱ የሚወክለው ሕወሃት ስንቶችን ለሀገር የሚያስቡ ሀገራዊ ድርጅቶችን በዘዴና በተቀነባበረ መንገድ በማጥፋት ፍጹም ጎጠኛነትን አስፋፍተዋል። እንደገና ዙረው ደግሞ ከኛ ሕወሃት በቀር ላሳር ይሉናል። በእርግጥ እንዲህ አይነት ጎጠኛና አጥፊ ቡድን በአፍሪካ ደረጃ ይኖር ይሆን? ለንጽጽር እንዲመች ስብሃትቢነግረን ጥሩ ነበር።

ዴሞክረሲያዊ ነኝ እያለ ዴሞክራሲአዊነትን የጨፈለቀ፤ ከአፍሪካ አገሮች ፍጹም በተለየ መልኩ ሰላማዊ እንቅስቀሴን ከስም በቀር መቶ በመቶ ያፈነ፤ መሰብሰብን በሰላመዊ ሰልፍ መሳተፍን እንዲሁም መደራጀትን ከስም በቀር በተግባር ያገደ ከሕወሃት በቀር ማን ሊኖር ይችላል? እኛ ካልመራን በቀር ሀገሪቱ ብርድ ብርድ ይላታል በሚል ልፍስፍስ አመለካከት በመታጠሩ የተነሳ ማንኛውንም በሀገር ውስጥ የሚገኝ ተቋም በራሱ ጠባብ ሰዎች ግጥም አድርጎ በመያዝ ሀገርም ሕዝብም የራሳችሁ ጉዳይ የሚል ከሕወሃት በቀር በእርግጥ በአፍሪካ አህጉር ሌላ ይገኝ ይሆን?

ስብሃት የቆጥ የባጡን የዘላበደለት ሕወሃትም ከተነገረለት ይልቅ በሽ ኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚገኝ ፍጹም ጎጠኛና ያልሰለጠነ አመለካከት የሚያራምዱ በቂም የተሞሉ ሰዎች ያቀፈ ቡድን ነው እንጅ እንደ ፓርቲ በአፍሪካ ደረጃ የሚወዳደር አይደለም።  ስለሆነም ስብሃት ነጋን “ሸንበቆ ስለረዘመ ምሰሶ አይሆንም” ልንለው እንወዳለን። ስብሃትም ሀነ ሌሎች ያሻቸውን ቢዘላብዱ ሸንበቆ ምሰሶ እንደማይሆነው ሁሉ ሕወሃትም ፈጣሪዎቹ ስላወሩለት ብዙ ብዙ ስለተናገሩለት ብቻ ጎጠኛነቱን ከፋፋይነቱን ትቶ እንደ አህጉራዊ ፓርቲ ይቅርና በሀገር ደረጃ እንኳ ለመታየት ብቃት ያለው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ደካማነቱን አምኖ መድረኩን ለውድድር ፍጹም ክፍት በማድረግ ብቃት ላላቸው ፓርቲዎች ቦታውን ማስረከብ ይጠበቅበታል።

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/7500

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s